ወባን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የአጋር አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተገለጸ።
ሐምሌ 08/2016ዓ.ም ሚዛን አማን
************
ወባን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የአጋር አካላት ተሳትፎ ወሳኝ ሚና እንዳለው በሚዛን አማን ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አዘጋጅነት ወባ መከላከልንና መቆጣጠርን መሰረት ያደረገ የፓናል ዉይይት ላይ ተገልጿል። ዉይይቱን በንግግር የከፈቱት የኮሌጁ ዲን አቶ ፀጋዬ አትርሴ እንዳሉት ኮሌጁ ከተቋቋመት ጊዜ ጀምሮ በተለያየ ሙያ መስኮች ተማሪዎችን እያሰለጠነ ወደ ማሕበረሰቡ እያሰማራ የሚገኝና በክልሉ ብቸኛ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ መሆኑን አስታዉሰው ከመማር ማስተማሩ በተጨማሪም ማሕበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ላይም በትጋት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። አክለዉም ኮሌጁ አሁን የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል የክልሉ ቲም ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ተማሪዎችንና መላው የኮሌጁን ማሕበረሰብ በማሳተፍ በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል። ወባን የመከላከሉን ስራና ተጨማሪ የማሕበረሰብ አገልግሎቶችን በስፋት ለመከወን ይርዳ ዘንድ ይህ ፓናል ውይይት መዘጋጀቱን ተናግረው ውይይቱ ወባን ለመከላከል የሚያስችሉ ስልቶችን በመንደፍ ክልሉ ወረርሽኙን ለመከላከል እያደረገ ያለዉን እንቅስቃሴ እንደሚያግዝም ጭምር ገልጸዋል።
የደ/ም/ኢ/ህ/ክ/መ/ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከልና ጤናን ማጎልበት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር እንዳለ ሳህሌ እንደተናገሩት ኮሌጁ ወባን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ካዘጋጀው መድረክ በተጨማሪ ከአካባቢ ንጽህና ጋር በየአከባቢው እያከናወነ ላለው ተግባር አመስግነው በ2030 ወባን ለማጥፋት ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደስራ የተገባ ቢሆንም ባለፉት ሶስት አመታት ግን ክልላችን ከፍተኛ የወባ ጫና እያስተናገደ ይገኛል ብለዋል። ክልላችን የልማት ኮሪደር በመሆኑ ምክንያት ለልማት የሚቆፋፈሩ ቦታዎች ዉሃ በማቆር ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ ያሉት ዶ/ር እንዳለ ለዚህም በክልሉ የማፋሰስና የማዳፈን፣ የአጎበር ስርጭት፣ የኬሚካል ርጭትና መሰል ተግባራት በስፋት እየተሰሩ መሆናቸዉን ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይም አራት ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች በኮሌጁ ምሁራን የተዳሰሱ ሲሆን ለአብነትም፡
- የሰው ልጅ ስነ ባህሪ ወባን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንፃር
- የአከባቢ ንፅህና ወባን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያለው ሚና
- ወባን ለመከላከልና ለመቆጣጠር መንግስትና ተቋማት ያላቸው ሚና
- ወባን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የማሕበረሰቡ ሚና
በሚሉ ርዕሶች የምሁራኑ ዳሰሳ ከቀረበ በኋላ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ሀሳቦች ተነስተው ውይይት የተካሄደባቸዉ ሲሆን የክልሉ ጤና ቢሮ የበሽታ መከላከልና ጤናን ማጎልበት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር እንዳለ ሳህሌ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በስተመጨረሻም የኮሌጁ ዲን አቶ ፀጋዬ አትርሴ፡ ወባ ከብዙ አመታት በፊት የነበረ በሽታ ቢሆንም አሁን ላይ ከወትሮው ከፍ ያለ ቁጥር በመታየቱ ምክንያት በሽታዉን በዘላቂነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲያስችል ይህ ፓናል ውይይት ከፍተኛ ሚና እንዳለው በመግለጽ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከውይይቱ በተነሱ የመፍትሄ ሃሳቦች ተግባራዊነት ላይ ተግተዉ እንዲሰሩ አበክረው ገልጸዋል። አቶ ፀጋዬ አያይዘዉም ይህንን ፓናል ውይይት ላዛጋጁት አካላት፣ ለተሳታፊዎችም ምስጋናቸዉን አቅርበው ለተገባራዊነቱም በትጋት እንደሚሰሩ ገልጸዋል። በፓናሉ ላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን የክልል አመራር፣ የቀበሌ አመራር፣ የኮሌጁ መምህራን፣ አስ/ር ሰራተኞች፣ ተማሪዎች እንዲሁም የሐይማኖት አባቶች ተሳትፈዉበታል።